Bible Verses by Topic

ተአምራት በብሉይ ኪዳን

1ኛ ነገሥት 18:19-40
አሁንም ልከህ እስራኤልን ሁሉ፥ በኤልዛቤልም ማዕድ የሚበሉትን አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፥ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ አለ። አክዓብም ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ ልኮ ነቢያቱን ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ። ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ። እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም። ኤልያስም ሕዝቡን አለ። ከእግዚአብሔር ነቢያት እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ የበኣል ነቢያት ግን አራት መቶ አምሳ ሰዎች ናቸው። ሁለት ወይፈኖች ይሰጡን፤ እነርሱም አንድ ወይፈን ይምረጡ፥ እየብልቱም ይቍረጡት፥ በእንጨትም ላይ ያኑሩት፥ በበታቹም እሳት አይጨምሩ፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረዋለሁ፥ በበታቹም እሳት አልጨምርም። እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን። ሕዝቡም ሁሉ። ይህ ነገር መልካም ነው ብለው መለሱ። ኤልያስም የበኣልን ነቢያት። እናንተ ብዙዎች ናችሁና አስቀድማችሁ አንድ ወይፈን ምረጡና አዘጋጁ፤ የአምላካችሁንም ስም ጥሩ፥ በበታቹም እሳት አትጨምሩ አላቸው። ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፥ ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ። በኣል ሆይ፥ ስማን እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር። በቀትርም ጊዜ ኤልያስ። አምላክ ነውና በታላቅ ቃል ጩኹ፤ ምናልባት አሳብ ይዞታል፥ ወይም ፈቀቅ ብሎአል፥ ወይም ወደ መንገድ ሄዶአል፥ ወይም ተኝቶ እንደ ሆነ መቀስቀስ ያስፈልገዋል እያለ አላገጠባቸው። በታላቅም ቃል ይጮኹ፥ እንደ ልማዳቸውም ደማቸው እስኪፈስስ ድረስ ገላቸውን በካራና በቀጭኔ ይብዋጭሩ ነበር። ቀትርም ካለፈ በኋላ መሥዋዕተ ሠርክ እስኪደርስ ትንቢት ይናገሩ ነበር፤ ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስና የሚያደምጥም አልነበረም። ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ። ወደ እኔ ቅረቡ አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ፈርሶ የነበረውንም የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ። ኤልያስም። ስምህ እስራኤል ይሆናል የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ ያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር አሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወሰደ። ከድንጋዮችም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚይዝ ጕድጓድ ቈፈረ። እንጨቱንም በተርታ አደረገ፥ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቈረጠ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረና። አራት ጋን ውኃ ሙሉ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ አሉ። ደግሞም። ድገሙ አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም። ሦስተኛ አድርጉ አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ። ውኃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ደግሞም ጕድጓዱን በውኃ ሞላው። መሥዋዕተ ሠርክ በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ። አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ። የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች። ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው። እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው አሉ። ኤልያስም። ከበኣል ነቢያት አንድ ሰው እንዳያመልጥ ያዙ አላቸው። ያዙአቸውም፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ ወስዶ በዚያ አሳረዳቸው።
30
Pause     Prev     Next